Header Topbar

ድምፅ አልባው ታዛቢ! The silent observer!

Thank you for reading this post, don't forget to subscribe!Thank you for reading this post, don't forget to subscribe!

ድምፅ አልባው ታዛቢ! The silent observer!

(ክፍል አንድ)

(እ.ብ.ይ.)

አውግቸው ከዘመኑ አስተሳሰብና ከዘመናዊው አኗኗር ጋር ተስማምቶ የሚኖር ደላላ ነው፡፡ ለዚህ ዓለም የተመቸ ባህርይ አለው፡፡ ደላላነቱ ከትንሽ ትልቁ ጋር ተግባብቶ እንዲኖር ረድቶታል፡፡ እውነቱን ለመናገር ማንንም ጓደኛ የማድረግ ክህሎት አለው፡፡ ቁመቱ አጭር ቢሆንም ፈጣን ነው፡፡ በዛ ላይ ጉራው ከቁመቱ ይረዝማል፡፡ አካሄዱ ሁለት አግሮቹን እኩል የሚያነሳቸው ነው የሚመስለው፡፡ ቅልጥፍናው አይጣል ነው፡፡ አውግቸውም ዓይነ-ገብ ነው፡፡ ቅላቱ ግርማሞገሱ ነው፡፡ የእኛ ሰው ቀይ ሰው ይወዳል፤ ሳያውቀው ያከብራል፡፡ ‹‹ቀይ ሰው መልክ አይፈጅም›› እያለ ቀዮችን ያደናንቃል፡፡

አውግቸው ምንም ቢቸግረው ኮትና ሱሪ አይቸግረውም፡፡ አለባበሱ ሁሌም የተዋጣለት ነው፡፡ የሰፈሩ ጎረምሶች ሲተርቡት ኮልፌ በመቶ ብር ብዙ ሱፎች የሚገዛ ሃብታም ነው ይሉታል፡፡ የሰልባጅ ደንበኛ ነው ማለታቸው ነው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ‹‹አውግቸው በልቶ ለድምፁ ነው›› ይሉታል፡፡ ሲናገር ጮክ ብሎ ስለሆነ ሃይሉን የሚጨርሰው በጩኸቱ ነው እያሉት ነው፡፡ ቀስ ብሎ ማውራት አይችልበትም፡፡ አውግቸው በማህበራዊ ኑሮው ላይ ንቁ ተሳታፊ ነው፡፡ በስራ ሰዓቱ አምስትኪሎ ከቅድስተማርያም ፊትለፊት ከሸዋ ዳቦ ቤት አጠገብ መገኛው ነው፡፡ የግል ቢሮ የለውም፡፡ ቢሮው ጎዳና ላይ ነው፡፡ ጓደኞቹ ሲያሙት ‹‹ትልቁ መዝናኛው በነፃ የሚዝናናበት ሰርግቤትና ለቅሶቤት ነው፤ ሰርግ ወይም ለቅሶ ከሌለ ላይ ሰፈር ካለው ጠጅ ቤት አይጠፋም›› ይሉታል፡፡

አውግቸው አላፊ አግዳሚውን ሰላምተኛ ነው፡፡ የማይወደድ ባህሪ ቢኖረውም ማንም አይጠላውም፡፡ ተጨዋችነቱ ደካማውን ባህሪ ሸፍኖለታል፡፡ ተረቡ፣ ለዛውና ቀልዱ በብዙ ሰዎች ዘንድ እንደአጫዋች ስለሚታይ ሃጢያቱን የሚቆጥርበት የለም፡፡ ምላሱ ሽሮ መብያው ነው፡፡ ውሸቱ፣ አምታችነቱ፣ ባዶ ተስፋ ሰጪነቱ እየታወቀ በማህበረሰቡ ዘንድ የተሰጠውን የክብር ቦታ አላስነጠቀም፡፡ እስከነውሸቱ ይወደዳል፤ እስከነአጭበርባሪነቱ ይከበራል፡፡ አውግቸው ለቤት ሰራተኝነት ወደእሱ የሚመጡ ስራፈላጊ ልጃገረዶችን በማማገጥ ይታወቃል፡፡ ኸረ እንደውም የቀመሳትን ስራ-ፈላጊ ሴት ሃብታም ቤት በጥሩ ደመወዝ ነው የሚያስቀጥራት እያሉ ያሙታል፡፡ አውግቸው እድለኛ ነው፡፡ የሚያታልለው ማህበረሰብ ሌብነቱን እያወቀበት እንኳን ይወደዋል፡፡ እየመዘበረው ያከብረዋል፡፡ ተሰሚነቱ ያስገርማል፡፡ ጉራው ይወደዳል፡፡ ይሄ ታዲያ ዕድል ወይም የመወደድ ግንባር ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

‹‹አስተዋይ›› የአውግቸው ጎረቤት ነው፡፡ ‹‹አስተዋይ›› ወዳጁም ሆነ ንብረቱ መፅሐፍ ነው፡፡ ብቸኝነትን ያዘወትራል:: ቤቱ አራትበአራት የሆነች በዕድሜ ብዛት ዘመም ያለች፣ ማገሮቿ የላሉ፣ ትንሽዬ የቀበሌ ቤት ነች፡፡ እሷም ብትሆን ከእናቱ የወረሳት ናት፡፡ በውስጧ አንድ ዘመዱ ከገጠር በስጦታ ያመጣለት በቀርከሃ የተሰራ የመፅሐፍ መደርደሪያ፣ ከእናቱ ያስቀረው አንድ የሽቦ አልጋ፣ ድክም ያለች ቡታጋዝ፣ ልብሶቹን የሚያስቀምጥበት ያረጀ ሳጥንና ላለፈው የዓለም ዋንጫ እቁብ ጥሎ የገዛት14 ኢንች ኮንካ ቴሌቪዝን ተጠጋግተውና ተደጋግፈው ተቀምጠውባታል፡፡ ቡታጋዝዋንም የሚጠቀመው መፅሐፍ ሲያነብ እንቅልፍ እንዳይጥለው ሻይ ለማፍላት ነው፡፡ ከዛ ወዲያ ቀለቡ ከውጪ ነው፡፡ ቤቱ ማንበቢያውና ማደሪያው ብቻ ነው፡፡ ሚስት የለው፤ ድስት የለው፡፡ ብዙ አያወራም፡፡ ንግግሩ ከራሱ ጋር ነው፡፡ ከሰላምታ ያለፈ ወሬ አይችልበትም፡፡ ዕትብቱ በተቆረጠበትና ከልጅነት እስከዕውቀት ባደገበት ሰፈሩ ከሚግባባው ሰው ይልቅ የማይግባባባው ይበልጣል፡፡ አንገቱን ደፍቶ ኗሪ ነው፡፡ ማህበራዊ ተሳትፎው እምብዛም ነው፡፡ ሰርግ ሲጠራ አይሄድም፡፡ ከሰፈሩ ጋር ዳመራ አይደምርም፤ ለግንቦት ልደታ ከጎረቤቶቹ ጋር አይሰበሰብም፤ በዓላት ላይ እስከዚህም ነው፡፡ አስረሽ ምቺው፣ ከቦ እየጠጡ መጨፈር፣ የዘመኑ ሰው ‹‹ላይፍ›› የሚለው ነገር አይመስጠውም፡፡ ማህበራዊ ጥሪ ላይ ከመሳተፍ ይልቅ ለእሱ ዛፍ ጥላስር ሆኖ ከራሱ ጋር ቢመሰጥ ይመርጣል፡፡ ‹‹አስተዋይ›› የአውግቸው ተቃራኒ ባህሪይ ነው ያለው፡፡ ሁለቱም አንድ ግድግዳ የሚለያቸው ጎረቤታሞች ናቸው፡፡ በዛ ላይ የመብራት ቆጣሪያቸው የጋራ ነው፡፡ ለአንድ አምፖሉ አራት አምፖልና አንድ የእንጀራ ምጣድ ካላቸው ከእነአውግቸው ጋር እኩል ነው የሚከፍለው፡፡ የመብራት ክፍያው ፍትሐዊና የተመጣጠነ እንዳልሆነ ቢያውቅም በይሉኝታ አብሮ ለመኖር ሲል ዝም ብሎ ይከፍላል፡፡

የ‹‹አስተዋይ›› ድምጽ አይሰማም፤ አውግቸው ግን ተኝቶም ዝም አይልም፡፡ ቀን የዋለበትን ሌሊትም በህልሙ ሲለፈልፍ ነው የሚያድረው፡፡ ‹‹አስተዋይ›› በአውግቸው ፀባይ ቢበሳጭም አንዳንድ ጊዜ ግን ባህርዪው ያዝናናዋል፡፡ ሰው እንዴት ዕድሜውን ሙሉ ከራሱ ጋር ተለያይቶ መኖር ይችላል ሲል ራሱን ይጠይቃል፡፡

‹‹አስተዋይ›› የአውግቸውን ቀጣፊነት በራሱ ደርሶ ያወቀው ለስራ ባልደረባው ሄኖክ የሚከራይ ቤት እንዲፈልግለት ካገናኘው በኋላ ነው፡፡ ከሄኖክ 400 ብር ቀብድ ተቀብሎት ክዶታል፡፡ በዚህ ጉዳይ ከሄኖክ ጋር ስላቆራረጠው ‹‹አስተዋይ›› አውግቸውን ታዝቦታል፡፡ በራሱ ላይ ብቻ ሳይሆን አውግቸው በቤተሰቦቹ ላይ የሚያደርሰውም በደል በየጊዜው በግድግዳው በኩል ስለሚሰማ ያናድደዋል፡፡ ጠጥቶ ሲመጣ ቤቱን በአንድ እግሩ ያቆመዋል፡፡ ሚስቱ እቴነሽን ካልደበደብኩ ብሎ የሰፈሩ ሽማግሌ የሆኑት አባባ አለማየሁ ናቸው የሚገላግሏቸው፡፡ በተለይ ቅዳሜና እሁድ የባልና ሚስቱ ድብድብ የተለመደ ነው፡፡

‹‹አስተዋይ›› በሰፈሩ ሰው ዘንድ ጥሩ ስም የለውም፡፡ ‹‹ይኮራል! ሰው አይቀርብም!›› ይሉታል፡፡ እኛ አሳድገነው እኛኑ ይንቃል እያሉ ያሙታል፡፡ ዝምታውን በንቀት ይተረጉሙበታል፡፡ ተግባቢ አለመሆኑን ከመረዳት ይልቅ ከክብር ጋር ያያይዙታል፡፡ በተለይ የዕድሜ አቻዎቹ ጋግርታሙ ፈላስፋ ይሉታል፡፡ በፊት ለሰርግ፣ ለልደት፣ ለክርስትና፣ ለጠበልጠዲቁ ሲጠሩት ስለማይሄድ አሁን ማንም አይጠራውም፡፡ ባለፈው አብሮአደጉና አንድ ክፍል አብራው የተማረችው ሔለን በመኪና አደጋ ሞታ ለቅሶ ለመድረስ ቤታቸው ቢሄድ ድንኳኑ ውስጥ የነበሩት የሰፈሩ ለቀስተኞች ሲጠቋቆምበት አይቶ ተበሳጭቷል፡፡ ኸረ እንደውም የሰፈሩ የሴት እድር ሊቀመንበር የሆኑት እትዬ ተዋበች ‹‹ዛሬ እንዴት መጣህ?›› ብለው በነገር ሸንቁጠውታል፡፡ ‹‹አስተዋይ›› የአካባቢው ሰው በእሱ ላይ ያለውን አመለካከት ሲያይ ሰፈሩን ጠልቶታል፡፡ ሁሌም ህልሙና ፀሎቱ ከሰፈሩ መገላገልን ነበር፡፡ ነገር ግን ባለፈው ያነበበውን የጀርመናዊውን ፈላስፋ የሾፐንሐወርን ታሪክ ሲያስታውስ ይፅናናል፡፡ ሾፐንሐወር አይደለም ባገሩ ሰው በእናቱ ጭምር ተገፍቶ የተጣለና የተጠላ እንደነበር ያስብና ራሱን ያነቃቃል፡፡ የእሱን ብቸኝነት ሲያስብ የሾፐንሐወር ብቸኝነት ትዝ ይለውና ይበረታታል፡፡ ፈላስፋው ያንን ሁሉ ጫናና መገለል ችሎ ትልቅ ደረጃ የደረሰው ስድባቸውንና ዘለፋቸውን አሸንፎ ነው ሲል ራሱን ይመክራል፡፡ ግን አንዳንዴ ሃሳቡን የሚረዳው ሲያጣ ትዝብቱንና ወቀሳውን በማያልቀው የሃሳብ ጅረቱ ያዥጎደጉደዋል፡-

‹‹አንዳንድ ጊዜ ሆድ ይብስሃል፡፡ በተለይ ከመጠን ያለፈ ትግስተኝነትህን እንደሞኝነት አድርገው የሚወስዱ ሰዎች ሲከቡህ ይከፋሃል፡፡ ብልጥ ሊሆኑብህ የሚሹ ገልቱዎችን ስታይ ሰው የሚባል ፍጡር ያስጠላሃል፡፡ ሰው እንዴት ራሱን ከመውደዱ የተነሳ ሌላውን መጥላት ደረጃ ላይ ይደርሳል? ራስን መውደድ ሌላውን የሚያስጠላ ሰበብ ሆኖ ስታገኘው ይገርምሃል፡፡ የግል ኑሮህ በአንድ በኩል ይንጥሃል፤ ከሰው ጋር አብሮ መኖር በሌላ በኩል ይፈታተንሃል፡፡ ራስህን ለመሆን የማትችልበት ዓለም ውስጥ እንዳለህ ሲገባህ የከተማ ባህታዊ ትሆናለህ፡፡ ቤትህን መመነኛ ባታህ ታደርጋለህ፡፡ድንዛዜዘቸውን ሊግቱህ ሲቋምጡ ከሃሳባቸው ሸሽተህ ባትህን ዘግተህ ትቀመጣለህ፡፡ ሽሽትህ አይገባቸውም፡፡ የሚረብሸው የዓለሙ ጩኸት ላንተ ከሩቅ ሆነህ የምትመለከተው ትዕይንት እንጂ መሃል ሆነህ የምትተውንበት የህይወት መድረክህ አለመሆኑን አይረዱልህም፡፡ ግፊያቸው፣ ትርምሳቸው፤ ግርግራቸው፣ ሩጫቸው ውጤቱ ሆድና ሆድ ብቻ ነው፡፡ ለመንፈሳቸው አያስቡለትም፡፡ ለልባቸው አይታመኑለትም፡፡ ነፍሳቸውን አስርበው ለከርሳቸው ሕይወታቸውን እየሰዉ ነው፡፡ በነሱ ግብስብስ ሕይወት እንድትማረክ ያማልሉሃል፡፡ እንካሰላንቴያቸው ይሰለችሃል፤ ፌዛቸው ይቸክሃል፡፡ ታጥቦ ያልጠራው ሃሳባቸው ያንተንም ሃሳብ ለማቆሸሽ በነሱ መንገድ ትመላለስ ዘንድ ይወተውቱሃል፡፡ ትዝብትህን፣ ብቸኝነትህን፣ ከራስ ጋር ተመካክሮ መኖርን፤ ከልብህ ጋር መደማመጥህን፤ ከመንፈስህ ጋር መግባባትህን፣ ምላስህን ቆልፈህ ነፍስህን ተናጋሪ ማድረግህን የማይወዱ የዚህ ዓለም አጋፋሪዎች ሊያጠምዱህ ይከታተሉሃል፡፡ ባንተ የግል ሕይወት እንደእርጎ ዝንብ ጥልቅ ሊሉ ይፈልጋሉ፡፡ እድል ሳትሰጣቸው፤ እንደወዳጅና ዘመድ ሳታማክራቸው ደርሰው ሃሳብ ሰጪና መካሪ ይሆናሉ፡፡ አስተያየት ሳትጠይቃቸው አስተያየት ይሰጡሃል፡፡ ያንተ የሕይወት መስመር ለእነሱ ያፈነገጠ ነው፡፡ እንደሐቁ ከሆነ እኮ እነሱ ናቸው ከሕይወት ያፈነገጡት፤ ራሳቸው ናቸው ከእውነት የተለያዩት፤ እነሱ አይደሉ እንዴ ማተባቸውን ሳያወልቁ የበጠሱት? እምነታቸው ከንፈራቸው ላይ የቀረው እኮ የነሱ ነው፡፡ አንተን ግን ፈጣሪውን የማያውቅ አድርገው ስም ይሰጡሃል፡፡ ነጠላ ተከናንቦ ቤተክርስቲያን መሳለም ብቻ መንፈሳዊነት ይመስላቸዋል፡፡ ፆም ለመቀበልና ፆሙን ለመፈሰክ ስጋ ቤት በር ላይ መሰለፍ ክርስትና ይመስላቸዋል፡፡ ሃይማኖታቸውን መሸሸጊያ እንጂ መኖሪያ አላደረጉትም፡፡ ከሰው ለመቀላቀል ሲሉ ብቻ ነው ሃይማኖተኛ የሚሆኑት፡፡ አኗኗራቸው ግን ከእምነታቸው የራቀ ነው፡፡›› እያለ ይወቅሳቸዋል፡፡

ዝም የሚል ሰው ተናጋሪ አዕምሮ እንዳለው የሚረዳ ሰው ጥቂት ነው፡፡ ታዛቢነት አሳቢነት መሆኑ የሚገባው እምብዛም ነው፡፡ መታዘብ አለሙን መመርመር፤ ከራስ ሃሳብ ጋር ማመሳከር መሆኑን የሚያውቅ ታዛቢ የሆነ ብቻ ነው፡፡ በርግጥ ዝምታ አንድም ምንጩ አለማወቅ ሊሆን ይችላል፤ አንድም የመናገሪያ ጊዜን መጠበቅ ሊሆን ይችላል፤ አንድም ከማትግባባው ሰው ጋር ከማውራት አለመናገር ይሻላል ከሚል አስተዋይነትም ሊመነጭ ይችላል፡፡ የሚናገረው የሌለው አላዋቂ ነው፡፡ የሚናገረው እያለው የሚናገርበትን ጊዜና ቦታ በመጠበቅ ዝም የሚል ሰው አዋቂ ነው፡፡ ‹‹አስተዋይ ሰው ዝም ይላል›› እንዲል መፅሐፉ፡፡

‹‹አስተዋይ›› በልቡ ከራሱ ጋር ማውራቱን አላቋረጠም፡፡ ብሶቱን የሚያወጣው፣ ስሜቱን የሚያስተነፍሰው፣ እፎይታ የሚያገኘው ከራሱ ጋር ሲነጋገር ነው፡፡ አዎ ትዝብቱንና ወቀሳውን ከራሱ ጋር እያወጋ ነው፡-

‹‹ተፈጥሮ የማያስተምራቸው፣ ዕድሜ የማይለውጣቸው ቆሞ ቀሮች፣ የቁስ ፍቅር የሚጋልባቸው የጥቅም ፈረሶች ዓላማቸው ቁስ፤ ድምዳሜያቸው ሁሉ ገንዘብን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ለእነሱ ክብር ያለው ገንዘብ፣ መኪና ፣ቤት፣ ዝና ያለው ነው፡፡ በቴሌቪዥን መስኮት በደግም ሆነ በክፉ የሚታይ ሁሉ ለእነሱ ዝነኛ ነው፡፡ ታዋቂና አዋቂ አይለዩም፡፡ ዘመናዊነትና ስልጣኔ ተምታቶባቸዋል፡፡ ሰውን እንደሰውነቱ የማክበር ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡ ቁስ ማግበስበስ፣ ነዋይ መሰብሰብ እንጂ ሌላ የሕይወት ህልምም ትልምም የላቸውም፡፡ አዕምሯቸውን የሚጠቀሙት የገንዘብ ወጪ ገቢ ለማስላት ብቻ እንጂ ስለህይወት፣ ስለሰውነት፣ ስለጥበብ፣ ስለመንፈሳዊ ፍሬ ተመራምረውና አውቀው ለመጠቀም አይደለም፡፡ በቃ አኗኗራቸውን ስታይ፣ ባህላቸውን ስትታዘብ፣ የሕይወት ፍልስፍናቸውን ስትገመግም ከእነሱ ጋር አልተገናኝቶም ነህ፡፡ የሚጨነቁበት አያስጨንቅህም፤ የሚያስደስታቸው አያስደስትህም፤ ሃሳባቸው ከሃሳብህ ጋር አይገጥምም፡፡ እኔ ሆንን ጠማማ የሆንኩት ብለህ ታስብና ራስህን ስትመረምር ካንተ ዘንድ የተጣመመ አስተሳሰብ እንደሌለ ታረጋግጣለህ፡፡ ሰው ምን ሆኖ ነው እንደዚህ የሆነው ትላለህ፡፡ በተለይ ትክክሉን በትክክለኛው ሰዓት በግልጽና በገሃድ ስትናገር እንቅፋቶችህ ይበዛሉ፡፡ ከብዙ አስመሳይ ሰው ጋር ትላተማለህ፡፡ ግጭት በግጭት ትሆናለህ፡፡ ፊትለፊት ተናጋሪነትሀ በሰው ዘንድ እንድትጠላ ያደርግሃል፡፡››

‹‹ብዙ ሰው ውስጥውስጡን መሄድን ለምዶታል፡፡ አስብቶ አራጅ ነው አካባቢህን የሞላው፡፡ ፊትለፊትህ እያቆለጳጰሰ ያሞቅሃል፤ ዘወር ስትል ይከታትፍሃል፡፡ የውሸት የሚያገጥብህ እንጂ የእውነት የሚስቅልህ ተመናምኗል፡፡ አንዳንዱ ዕድልና ጊዜ ገጥሞት ውለታ ይውልልህና ባሪያው እንድትሆን ይፈልጋል፡፡ እንደው ስለውለታው ብለህ እንዳልገባው ሆነህ ብትታገሰውም የአንተን ትዕግስት ከሞኝነት ይቆጥረዋል፡፡ ዘወትር የእሱን ውለታ እያሰብክ እንድታሸረግድለት የሚፈልግ የውለታ ነጋዴ ብዙ ነው፡፡ ጊዜህን የገዛው፤ አንተነትህን የተከራየው ይመስለዋል፡፡ የራስህ ጊዜ፣ የራስህ ፕሮግራም፣ የራስህ ነፃነት፣ የራስህ ፈቃድ እንዳለህ አይረዳም፡፡ በእሱ ፍላጎትና እቅድ ሊሾፍርህ ይሻል፡፡ ባጣ ቆየኙ አድርጎህ ሲፈልግህ ብቻ የሚያገኝህ መደበሪያው ሊያደርግህ ይጥራል፡፡ አጃኢብ የኛ ሰው››

ይቀጥላል……

(እ.ብ.ይ.)

ድምፅ አልባው ታዛቢ! The silent observer!
Spread the love
Scroll to top

You cannot copy content of this page