Header Topbar

ድምፅ አልባው ታዛቢ! The silent observer! – Part 2

ድምፅ አልባው ታዛቢ!

Thank you for reading this post, don't forget to subscribe!Thank you for reading this post, don't forget to subscribe!

(ክፍል – 2)

አራት ኪሎ

የአዲስ አበባ ሰማይ እንደአብዛኛው ነዋሪ አስመሳይ ነው፡፡ ፈካ ስትለው ይደበዝዛል፤ ሞቀ ስትለው ይቀዘቅዛል፡፡ ዳመና አርግዞ በንፋስ ይበትነዋል፡፡ ጠራራ ፀሐይ ወጣ ስትል ጣሪያ የሚበሳ በረዶ ይጥላል፡፡ አሪፍ ቀን ሆኗል ብለህ ያልታሰብ ዝናብ መጥቶ ያበሰብስሃል፡፡ በዚህ ጊዜ ሰማዩንም ሜትሮሎጂውንም ማመን አደጋ አለው፡፡ የሸገር ዝናብ ጣጣው ብዙ ነው፡፡ ሐይለኛ ዝናብ ሳያቋርጥ በትንሹ ለ15 ደቂቃ ከጣለ አስፋልቱ ሁሉ ወንዝ ይሆናል፡፡ ጎርፉ ይጎርፋል፤ ከተማው ይጥለቀለቃል፡፡ የከተማው ትርምስ ይጨምራል፤ ትራንስፖርቱ ይስተጓጎላል፤ መብራቱ ይጠፋል፤ ኔትዎርኩ ይቋረጣል፤ ችግሩ ይከታተላል፡፡ በዛ ላይ ባለመኪናውም እንደጠበል ጎርፉን እየረጨህ፣ ልብስህን እያበላሸ ነው የሚያልፈው፡፡ ይሄን ሲያደርግ የጀግንነት እንጂ የመሳቀቅና የስህተት ስሜት አይታይበትም፡፡ ‹‹እንደእኔ መኪና አትገዛም ነበር›› የሚል ዕቡይነት ያለው መልክ አሳይቶህ ያልፋል፡፡ አይደለም የግል መኪና ባለቤት መሆን ቀርቶ የመንግስት መኪና ሾፌርም ሆነው ጉራቸው የትየለሌ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የሚያስገርመው በጎ ሰው መሆን ብቻ ነው፡፡ ክፋት በሰለጠነበት ምድር አንድ ቀና ሰው ከተገኘ ጉድ ማለት ተለምዷል፡፡ ምክንያቱም ሌላውን ማስቀደም፣ መተዛዘን ቀርቷል፡፡ ትህትና፣ ለሌላው ማሰብ፣ ደግ መሆን ፋሽን ያለፈባቸው ሆነዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዝናቡ ካቆመ በኋላ ወዲያው በእግር ለመንቀሳቀስ ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም አስፋልቱ በጎርፍ ይጥለቀለቃል፤ በዛ ላይ የአዲስአባባን የጓዳ ገበና አስፋልቱ ላይ ይዘረግፈዋል፡፡ ከአንዱ የአስፋልት ጫፍ ወደሌላኛው ጫፍ በራስ ለመሻገር አይቻልም፡፡ ወይ ለደቂቃዎች መጠበቅ ያስፈልጋል አልያም አሻጋሪ ግድ ይላል፡፡ በዚህ ችግር ሳቢያ አንዳንዶች ጭንቅላታቸውን በመጠቀም የአሻጋሪነት ቢዝነስ ፈጥረውበታል፡፡ የአስፋልት ላይ ወንዙን ሰው አዝሎ በማሻገር ገንዘብ ያገኙበታል፡፡ የከተማው አስተዳደር ወንዞችን የማልማት ፕሮጀክት አለኝ ቢልም የአስፋልት ላይ ወንዞችን ግን አላካተተም፡፡ በመንግስት የተረሱ አያሌ ችግሮች በከተማችን ሞልተዋል፡፡ ለነገሩ አይደለም መሰረተልማቱ ቀርቶ አብዛኛው የከተማው ነዋሪ በመንግስት ተረስቶ የለ እንዴ! ምን ያስደንቃል! አዲስአበቤው ለግብር ክፍያና ለድጋፍ ሰልፍ ከተፈለገ ይበቃዋል!

መሠረት ከቤቷ የወጣችው ዝናቡ ሳይጀምር ነበር፡፡ ጃንጥላ እንኳን አልያዘችም፡፡ አለባበሷም ቢሆን ለዝናብ የሚሆን አይደለም፡፡ ከላይ ግራጫ መልክ ያለው ስስ ቦዲ፣ ከታች ቀይ ጉርድ ቀሚስ ነው የለበሰችው፡፡ ጫማዋም ቢሆን ዝናብ ሊያስገባ የሚችል የበጋ ጫማ ነው፡፡ መሰረት ከጌጣጌጥ ነፃ ነች፡፡ ኩል አትኳልም፡፡ ሜክአፕ ፊቷን ነክቷት አያውቅም፡፡ ፈጣሪ የለገሳትን ውበቷን ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ነው የምትንከባከበው፡፡ ተጨማሪ ነገር አትጠቀምም፡፡ ከጠይም መልኳ ጋር ስትታይ የሃበሻ ንግስት ትመስላለች፡፡ ጉርድ ቀሚስ ያምርባታል፡፡ እንደአብዛኞቹ ሴቶች ሱሪ አትለብስም፡፡ ፀጉሯን እንደነገሩ ብትለቀውም ርዝመቱ ብቻውን የሰውን ዓይን ይስባል፡፡ ራሷ ሸጣ ቢዝነስ ካልሰራች በቀር የሂውማን ሄር ወጪ የለባትም፡፡ ምክንያቱም አምላክ ድንቅ ፀጉር ከሚያምር ቁመና ጋር አድሏታል፡፡ ምንም እንኳን አለባበሷ የተለመደ ቢሆንም ዛሬ ግን ፊቷ ፈክቷል፡፡ የተደበቀው ውበቷ በርቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ከሰው ጋር ቀጠሮ ተቀጣጥራ በሰዓቱ መገኘት አይሆንላትም ነበር፡፡ ዛሬ ግን ከቀጠሮዋ ሰዓት በፊት አንድ ሰዓት ቀድማ ነው ከቤቷ የወጣችው፡፡ ምን ዋጋ አለው! ዝናቡ አሰናክሏታል፡፡

በርግጥ የመስከረም ወር አሳሳች ነው፡፡ ዝናቡ ጨርሶ ያላቆመበት፤ ፀሐዩም ሙሉ በሙሉ ያልወጣበት ስለሆነ ብዙ መልክ ነው ያለው፡፡ አንዴ ዝናብ፤ አንዴ ፀሐይ! አንዴ እርጉዝ ዳመና! አንዴ ጨለምለም ያለ ቀን! የአዲስአበባ አየር ዓመሉን ነዋሪው ላይ አጋብቷል፡፡ አንዳንድ ሰው የመስከረምን ወር ይመስላል፡፡ አንዴ ጥሩ ፊት ያሳይህና፤ ምክንያቱን ባላወቅከው ነገር ፊቱ ወደክረምትነት ይለወጥብሃል፡፡ በፈገግታ ተቀብሎህ በቁጣ የሚሸኝህ ብዙ ሰው አለ፡፡ በሞቅታ አስተናግዶህ ከደቂቃዎች በኋላ ብርድ ብርድ የሚለው ሺ ነው፡፡ በርግጥ ግጭቱ ካንተ ጋር አይደለም፡፡ ከራሱ ጋር ነው! ከራሱ ጋር የተጋጨ ወጥ የሆነ መልክ የለውም፡፡ በየሰከንዱ ፊቱ የሚለዋወጥ፤ በየደቂቃው ባህሪው የሚገለባበጥ ሰው ጠቡ ከራሱ ጋር ነው፡፡ መቀያየሩ ለራሱ እንኳን የማይታወቀው፤ ደመነፍሱ የሚሾፍረው፤ ስሜቱ የሚነዳው ሰው የዓለሙ ሁኔታ ባህሪውን ከፍ ዝቅ ያደርገዋል፤ ኑሮውን ያናጋዋል፤ ሕይወቱን ያጥበረብረዋል፡፡ ቆም ብሎ ማሰብ አልተለማመደም፡፡ የመጣው ወጀብ እንዳሻው ይወስደዋል፡፡ ደስታው ቅጽበታዊ ነው፡፡ የሚስቀው ከላይ እንጂ ከልቡ አይደለም፡፡ ሳቁና ለቅሶውን ለመለየት ያስቸግራል፡፡ በአንድ ጊዜ ግምባሩ ተቋጥሮ ይፈታል፤ እንደገናም ተፈትቶ ይቋጠራል፡፡ የተዘበራረቅና ያልተረጋጋ ማንነት!

መሠረት ያ ሁሉ ዶፍ ዝናብ ሲጥል አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኝ አንድ ካፌ ውስጥ ነበረች፡፡ እዚህ ካፌ ውስጥ ከዚህ ቀደም ገብታ አታውቅም፡፡ ዝናቡ ነው አሯሩጦ ያስገባት፡፡ ካፌው ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ በሰው ተጨናንቋል፡፡ አይደለም መቀመጫ ቀርቶ መቆሚያ ቦታ የለውም፡፡ መሰረት ግን አንድ ጥግ ቦታ ላይ የተቀመጠ ወጣት በምልክት ጠርቷት ተነስቶ አስቀመጣት፡፡ በጊዜው አላመሰገነችውም ነበር፡፡ ከተረጋጋች በኋላ ግን ለምን እንዳላመሰገነችው አስባ ፀፀት ተሰማት፡፡ ሰውየው በቁሙ በእጁ መፅሐፍ ይዞ እያነበበ ነበር፡፡ በራሷ ተናደደች፡፡ እያንዳንዷን ትናንሽ መልካምነት ካላመሰግንን እንዴት ትላልቅ መልካም ነገሮችን ልናገኝ እንችላለን በማለት ከራሷ ጋር ሙግት ያዘች፡፡ ከዛ እንደምንም ብላ፡-

‹‹አመሰግናለሁ ወንድሜ!›› አለችው፡፡ ወጣቱ ምስጋናዋን ‹‹ችግር የለውም!›› በሚል አጭር ቃል መለሰላት፡፡

ቆይቼ ስላመሰገንኩት ነው በአጭሩ የመለሰልኝ ወይስ ምስጋናዬን አቅልሎት ነው ብላ አሰበች፡፡ አይ ቀድሞውኑ መቀመጥ ሰልችቶት መቆም ፈልጎም ሊሆን ይችላል የተነሳልኝ፡፡ የወጣቱ መልስ መሠረትን ብዙ አሳሰባት፡፡ ወጣቱ ረዘም ያለና ቅንድቡ ግጥም ያለ ነው፡፡ አለባበሱ መካከለኛ ነው፡፡ ፊቱ ከሳ ያለ ቢመስልም በራስ መተማመን ያለው ይመስላል፡፡ ጥቁር ጫማ ተጫምቷል፡፡ ኦሞ ከለር ጅንስ ለብሷል፡፡ ከላይ ቀይ ቲሸርት ብቻ ነው ያደረገው፡፡ እሱም እንደእኔ ፀሐይ ነው ብሎ አስቦ ነው ከቤቱ የወጣው  ብላ አሰበች፡፡ ቀና ብላ ስታየው ዓይናቸው ተገጣጠመ፡፡ ወዲያው ዓይኑን ወደመፅሐፉ መለሰ፡፡ አይናፋር ይሆን ብላ አሰበች፡፡ መሰረት ሳታስበው ስለማታውቀው ሰው ደጋግማ ማሰቧ ገረማት፡፡ ቁመናውን፣ ሁኔታውን፣ መልኩን፣ ሁሉ ነገሩን መገምገም ጀመረች፡፡ የያዘውን መፅሐፍ ርእስ ለማንበብ አጮልቃ ብታይም ለማየት አልተመቻትም፡፡ ወጣቱ የመፅሐፉን ርዕስ ለማየት እንደፈለገች ሲገባው፡-

‹‹ርዕስ አልባው መፅሐፍ›› ይባላል አላት፡፡ ‹‹ምን?›› አለችው በመገረም፡፡ ቀጥላም ‹‹ርዕስ አልባ መፅሐፍ እንዴት ርዕስ ሊሆን ይችላል?›› ‹‹ማለቴ ርዕስ አልባ ከሆነ ራሱ እንዴት ርእስ ሊሆን ይችላል?›› አለች የፈጠረባትን ግራ በመጋባት በመግለፅ፡፡ ወጣቱ ስለመፅሐፍ ሲነሳ ፊቱ ይፈካል፡፡ በተለይ ስለመፅሐፍ የምትወያይ ሴት ያደንቃል፡፡ እንደእሱ አመለካከት ብዙ ሴቶች ትርኪምርኪ ወሬ ላይ ነው ጊዜአቸውን የሚያጠፉት፤ የሚያስጨንቃቸው እንቶ ፈንቶ ነው፡፡ እከሌ አገባ፣ እከሊት ፈታች፤ እንትና መኪና ገዛች፣ ያ ማነው ዱባይ ሄዶ ተንሸራሸረ፣ ያረገው ጫማ፣ የያዘችው መኪና፣ የገዛው ቤት ወዘተ ለሚሉ ቁሳዊ ወሬዎች ነው ሴት ትኩረት የምትሰጠው፡፡ ቦርሳቸውንም አዕምሯቸውንም የሞላው ኮተት ነው ብሎ ነው የሚያስበው፡፡ ይቺ ሴት ግን ተለየችበት፡፡ በዛ ላይ ጥያቄዋ የሚያፈላስፍ ትልቅ ቁምነገር ያለው ነው፡፡ ወዲያው ስሜ ‹‹አስተዋይ ይባላል!›› አላት፡፡ መሰረት ደነገጠች፡፡ ያ ሲርየስ የነበረው ወጣት ፊቱ ፈክቶ በደስታ ስሙን ሲነግራት ደነቃት፡፡ እሷም ያለማመንታት ‹‹ መሰረት›› እባላለሁ አለችው፡፡

አስተዋይ የመሰረት ጥያቄ አዲስ ሃሳብ ጫረለት፡፡ ሃሳብ የሚያስነሱ ሃሳቦች ይመቹታል፡፡ ለማሰብ የሚያነሳሱ ቀስቃሽ ቃላቶች ስሜቱን ይነሽጡታል፣ የጥበብ ብልቱን ይቀሰቅሱታል፡፡ ከቃላት ጋር መፋጠጥ፤ ከሃሳብ ጋር መስመጥ፣ በማሰላሰል መጥለቅ የኖረበት ነው፡፡ ሁሌም ስለሃሳብ ሲያስብ ማሰብን ያስቻለ፤ የሚታሰበውን ሃሳብ የፈጠረ አምላክ ክብር ይገባዋል ይላል፡፡ የሚታሰብ ሃሳብ ያላሳጣ አምላክ ይመስገን ይላል፡፡ ከሚታየውና ከሚሰማው በላይ የሚታሰበው እንደሚልቅ ያምናል፡፡ የመፅሐፍ ርዕስ መስጠት ከባድ ነገር ነው፡፡ ለአንድ ሰው ደግሞ ርዕስ ስጡ ቢባል የሚቻል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሰው በየሰዓቱ ማንነቱ ይለዋወጣል፡፡ ትናንት ያፀደቀውን ሃሳብ ዛሬ ሊሽረው ይችላል፡፡ አሁን የሚያቀነቅነውን ፍልስፍና ነገ ይኮንነዋል፡፡ የሰው ሕይወቱ በትናንቱ ብቻ አይለካም፡፡ ትናንት እንዲህ ነበር ለማለት ራሱ በየትኛው ትናንቶቹ የሚለው በጥልቅ ሊገለፅ ይገባል፡፡ ሰው ስምና ርዕስ የሚሰጠው እየጀመለ ነው፡፡ የሆነውንም ያልሆነውንም በሚደመድም ዓለም ውስጥ ርዕስ መስጠት ቀላል ነው፡፡ ለአሳቢ ሰው ግን ስምና ርዕስ መስጠት ትልቅ ምርምር የሚሻ የቤት ስራ ነው፡፡ ለዚህ ይሆናል ይሄን መፅሐፍ የፃፈው ሰው ‹‹ርእስ አልባው መፅሐፍ›› ያለው፡፡ አስተዋይ ይሄን መፅሐፍ የገዛው በርካሽ ነው፡፡ አራት ኪሎ ጀሊ ባር ፊትለፊት የተለመደውን የጋዜጣውንና የመፅሔት የግረባ ሱሱን ተወጥቶ ወደቤቱ ሲያቀና መሬት ዘርግተው በርካሽ ከሚሸጡ መፅሐፍት መካከል ይሄ መፅሐፍ ርዕስ የሌለኝ ነኝ ብሎ በዓይን ጥቅሻ ጠራው፡፡ ርእሱ ብቻ ስለሳበው አነሳና ገዛው፡፡

አስተዋይ ከሃሳብ ዓለሙ መለስ ብሎ ‹‹ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ያነሳሽው ሃሳብ ብዙ እንዳስብ አድርጎኛልና አመሰግናለሁ›› አላት፡፡ መሰረትም ለመልሱ ጓግታ ‹‹እኔም አመሰግናለሁ›› አለች፡፡  አስተዋይ መፅሐፍ ሲያነብ የደራሲውን ሃሳብ ከተረዳ በኋላ በሃሳቡ ላይ ያለውን ምልከታ ያስቀምጣል፡፡ ድጋፍም ቢሆን እንኳን በተለየ ሃሳብ ነው መደገፍ የሚፈልገው፡፡ የደራሲውን ሃሳብ መድገም አይወድም፡፡ የተቃርኖ ሃሳብ ከሆነ ደግሞ ሃሳቡን በማስረጃ አስደግፎ የመተንተን ብቃት አለው፡፡ የሚያነበውን ሲፅፍ፤ የፃፈውን ሲያነብ ነው የኖረው፡፡ መፃፍና ማንበብ፣ ማንበብና መፃፍ የእለት ተዕለት ሕይወቱ አድርጎታል፡፡

አስተዋይ ወደመሰረት ዓይኑን መልሶ፡-

‹‹ደራሲው በገፅ 8 ምን ይላል መሰለሽ›› ‹‹ርዕስ አልባው መፅሐፍ ሲከፈት ሚስጥሩ፤ በቀለም ሲጋለጥ ርዕስ ሆኖ የተገኘው ራስ ነው፡፡ ያልተነበበው መፅሐፍ ሰው መሆኑ ነው›› ይልና በዚሁ ገፅ ላይ የመፅሐፍትን ርዕስ በሁለት መንገድ ማውጣት እንደሚቻል ይገልፃል፡፡ ይኸውም አንድም መፅሐፉን ከርዕሱ ማግኘት፤ አንድም ከመፅሐፉ ርእሱን ማውጣት፡፡››

መሰረት ይሄን መሳጭ ውይይት ስታካሂድ የሰዓቱ መሄድና የዝናቡን ማቆም ውል አልሰጠችውም ነበር፡፡ የእጇን ሰዓት ስትመለከት ከቀጠሮዋ ሰዓት አስር ደቂቃ አልፏል፡፡ ወዲያው ደንገጥ ብላ፡-

‹‹ይቅርታ አስተዋይ…  ውይይታችንን ሌላ ጊዜ መቀጠል እንችላለን፡፡ አሁን አስቸኳይ ቀጠሮ አለብኝ፡፡ ስለሃሳብህና ስለክብርህ በጣም አመሰግናለሁ›› ብላ ከቦርሳዋ የስልክ ቁጥሯንና የስራ አድራሻዋ ያለበትን የቢዝነስ ካርድ አውጥታ ሰጠችው፡፡ ‹‹በማንኛውም ሰዓት ብትደውልልኝ ማውራት እንችላለን›› ብላ የሱን መልስ ሳትጠብቅ ተሰናብታው ወጣች፡፡

(እ.ብ.ይ.)

ይቀጥላል……

ድምፅ አልባው ታዛቢ! The silent observer! – Part 2
Spread the love
Scroll to top

You cannot copy content of this page