መመሪያ ቁጥር 1110/2018
የደመወዝ ስኬል ማሻሻያ አፈጻጸም መመሪያ
Thank you for reading this post, don't forget to subscribe!Thank you for reading this post, don't forget to subscribe!
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በፌዴራል መንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 አንቀጽ
156 (2) መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል።
ክፍል አንድ ጠቅላላ
1. አጭር ርእስ
ይህ መመሪያ “የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የደመወዝ ስኬል ማሻሻያ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1110/2018” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
2. ትርጓሜ
1) የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ ማለት የአንድን ሠራተኛ ደመወዝ ወደ አዲሱ የደመወዝ ስኬል ለማሸጋገር ሲባል ቅርበቱ እየታየ የነበረውን ደመወዝ እንደሁኔታው ወደ አዲሱ የደመወዝ ስኬል የመነሻ፣ የእርከን ወይም የጣሪያ ደመወዝ ላይ ለማሳረፍ የሚፈቅድ የደመወዝ ማሻሻያ ነው።
2) ኮሚሽን ማለት የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ነው።
3) በዚህ መመሪያ ውስጥ ማንኛውም በወንድ ጾታ የተገለጸ የሴት ጾታንም ያካትታል፡፡

ክፍል ሁለት
3. በመንግስት ውሳኔ የተሰጠባቸው ጉዳዮች
1) የደመወዝ ማሻሻያ ክፍያው በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ ከመስከረም 1 ቀን
2018 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡
- ይህ መመሪያ በ2018 ዓ.ም እየተደረገ ባለዉ የደመወዝ ስኬሎች ማስተካከያ ላይ ብቻ ተፈጻሚ ይሆናል።
- የደመወዝ ማሻሻያዉ የመንግስት ሰራተኞችን፣ ተሿሚዎችን፣ የፀጥታና ደህንነት አካላትን እና በልዩ ህግ የሚተዳደሩ ተቋማትን ያካትታል፡፡
- በተነፃፃሪ የተሻለ የደመወዝ ክፍያ የሚከፈላቸዉ በሲቪል ሰርቪስ ህግም ሆነ በልዩ ህግ የሚተዳደሩ አካላትን ይህ የደመወዝ ማሻሻያ ላይመለከታቸዉ ይችላል
- ለልዩ ደመወዝ ስኬል ተጠቃሚዎች የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የመንግስት ሠራተኞችን የደመወዝ ስኬል ማሻሻያ መጠን መሠረት በማድረግ የደመወዝ ስኬል ማሻሻያ እና የመሸጋገሪያ ሠንጠረዥ አዘጋጅቶ ያስተላልፋል፡፡
- የተደረገው የደመወዝ ማሻሻያ ከፍተኛ ወጪ የሚያስከትል በመሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አቅጣጫ ካልተሰጠ በስተቀር በዚህ የበጀት ዓመት በየትኛውም ደረጃ ባሉ የመንግሥት እና በልዩ ህግ በሚተዳደሩ ተቋማት ምንም ዓይነት የደመወዝ ስኬል ማሻሻያ ጥያቄ አይስተናገድም፡፡
- ወርሃዊ ደመወዛቸው ብር 42,000 እና በላይ የሆናቸው የመንግስት ሠራተኞች፣ በዚህ ጥናት ያልተካተቱ በመሆኑ ይህ መመሪያ ተፈጻሚ አይሆንባቸውም፡፡

ክፍል ሶስት
ዝርዝር አፈጻጸም
4. የደመወዝ ማሻሻያውን በሚመለከት መንግሥት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች መሠረት በማድረግ የተዘጋጀው የአፈጻጸም መመሪያ ከዚህ ቀጥሎ ቀርቧል፡፡
1) የደመወዝ ማሻሻያ ተጠቃሚ የሚሆኑ የመንግስት ሠራተኞች ባገኙት የደመወዝ
ማሻሻያ ምክንያት፡-
ሀ) የመደበኛ የደመወዝ ጭማሪ ኡደታቸው አይለወጥም፡፡
ለ) ለደረጃ እድገት የአንድ ዓመት መቆያ ጊዜ ማሟላት አይጠበቅባቸውም፡፡
2) ከፍ ባለ የሥራ ደረጃ ላይ በተጠባባቂነት የተመደበ ሠራተኛ የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ ልዩነት የሚታሰብለት በድልድሉ በተመደበበት ደረጃ ላይ ነው፡፡
3) በጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም ተሻሽሎ በሥራ ላይ በዋለው ወይም አግባብ ባለው አካል በተፈቀደ የደመወዝ ስኬል ጣሪያ ላይ የደረሰና በአዲሱ የደመወዝ ስኬል ጣሪያው የሚነሳለት ሠራተኛ በተመደበበት የሥራ ደረጃ የአዲሱን የደመወዝ ስኬል ጣሪያ ሳያልፍ ማሻሻያውን እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡
4) ኮሚሽኑ በአንድ ተቋም ከተፈጸሙ የሠራተኞች ድልድል ወይም የደረጃ እድገት መካከል በተለያዩ ሕግን ባልተከተሉ አሠራሮች ምክንያት ያልተቀበለው ካለ
የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ ጭማሪው የሚሰጠው በድልድል አፈጻጸም መመሪያው መሠረት ሠራተኛው በሚያሟላበት ደረጃ ከተደለደለ በኋላ ነው፡፡
5) ከፍ ካለ የሥራ ደረጃ ላይ በሚታሰብ ደመወዝ ተቀጥሮ ወይም ተመድቦ እየተቀነሰ የሚከፈለው ሠራተኛ የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ ተጠቃሚ የሚሆነው በሚያሟላበት ደረጃ ላይ ተመሥርቶ ይሆናል፡፡

6) በሙከራ ቅጥር ላይ የሚገኝ ሠራተኛ የዚህ የደመወዝ ስኬል መሸጋገሪያ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
7) በዲሲፕሊን ጉድለት ምክንያት ከደረጃው ዝቅ ያለና ደመወዙ የተቀነሰበት ሠራተኛ ማሻሻያው የሚሰጠው በተቀነሰው ደረጃና ደመወዝ ላይ ታስቦ ነው፡፡ ሆኖም በተወሰነ የጊዜ ገደብ ከደረጃና ደመወዝ ዝቅ የተደረገ ሠራተኛ የጊዜ ገደቡ ደርሶ ወደ ቀድሞ ደረጃው ሲመለስ ከተመለሰበት ጊዜ ጀምሮ በአዲሱ የደመወዝ ስኬል ተገቢው ደመወዝ ይሰጠዋል፡፡ ያለደመወዝ ልዩ ፈቃድ ተሰጥቶት በፕሮጀክት አፈፃፀም መመሪያ መሠረት ወደ ፕሮጀክት የተዛወረ ወይም በፕሮጀክት የተቀጠረ ሠራተኛ ወደ መደበኛ ሥራው ሲመለስ ወደ ፕሮጀክት ከመዛወሩ በፊት በነበረበት የሥራ መደብ /ደረጃ/ የተወሰነው አዲሱ ደመወዝ ተጠቃሚ ይሆናል።
8) ያለደመወዝ ልዩ ፈቃድ ተሰጥቶት በፕሮጀክት አፈጻጻም መመሪያ መሠረት ወደ ፕሮጀክት የተዛወረ ወይም በፕሮጀክት የተቀጠረ ሠራተኛ ወደ መደበኛ ሥራው ሲመለስ ወደ ፐሮጀክት ከመዛወሩ በፊት በነበረበት የሥራ መደብ (ደረጃ) የተወሰነውን አዲስ ደመወዝ ተጠቃሚ ይሆናል።
9) ይህ የደመወዝ ስኬል ማሻሻያ ጊዜያዊ ወይም የኮንትራት ወይም የፕሮጀክት ሠራተኞችን ይመለከታል፡፡ በኮሚሽኑ ተመዝኖ ደረጃ በወጣለት ወይም በቋሚ የሥራ መደብ ላይ መመሪያውን ተከትሎ የተቀጠረ ጊዜያዊ ወይም የኮንትራት ሠራተኛ ወይም በሚመለከተው አካል በተፈቀደ የፕሮጀክት ደመወዝ ወይም ልዩ የደመወዝ ስኬል የተቀጠረ ጊዜያዊ ወይም የኮንትራት ሠራተኛ የደመወዝ ማሻሻያ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
10) በተለያዩ ምክንያቶች ከመደበኛ ሥራው ተለይቶ የቆየ ሠራተኛ ወደ ሥራው እንዲመለስ ሲደረግ ተመዝኖ ደረጃ በወጣለት የሥራ መደብ ላይ እንዲመደብ ከተደረገ በኋላ ደመወዙ ወደ አዲሱ የደመወዝ ስኬል እንዲሸጋገር ይደረጋል፡፡

11) በሥራው ልዩ ባህርይ ምክንያት እያስተማረ የህክምና አገልግሎት የሚያበረክት የጤና ባለሙያ የማስተማር ሥራው እንደተጠበቀ ሆኖ በአካዳሚክ ወይም በጤና ሙያ /ከፍ ባለው/ ደረጃ ላይ ብቻ ማሻሻያው ይከፈለዋል፡፡
12) በአደረጃጀት ለውጥ ምክንያት በትርፍነት ተይዘው በመንግሥት ሠራተኞች የድልድል አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 859/2014 መሠረት ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት እስኪመደቡ ደመወዝ እየተከፈላቸው ያሉ ደመወዛቸው ወደ አዲሱ የደመወዝ ስኬል እንዲሸጋገር ይደረጋል፡፡
13) አግባብ ባለው አካል ባልተፈቀደ ልዩ የደመወዝ ስኬል እና በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ተመዝኖ ደረጃ ባልወጣለት የሥራ መደብ ላይ የደመወዝ ማሻሻያ መፈጸም በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡
14) በማንኛውም ህጋዊ ምክንያት ከነበረበት የሥራ ደረጃና ደመወዝ ዝቅ ተደረገ ሠራተኛ የደመወዝ ማሻሻያው ዝቅ ባለው የሥራ ደረጃ ይሠራለታል፡፡
15) ከመስከረም 2018 ዓ.ም ጀምሮ በነባሩ የደመወዝ ስኬል የሠራተኛ ስምሪት መፈጸም አይቻልም፡፡
16) ልዩ የደመወዝ ስኬል የተፈቀደላቸው ተቋማት ከብር 42,000 በታች ላሉ የመነሻ፣ የእርከን ወይም የጣሪያ ደመወዞች የደመወዝ ማሻሻያ የተደረገ ሲሆን፣ ብር 42,000 እና በላይ የነበሩ ደመወዞች በደመወዝ ስኬሉ ላይ እንደነበሩ የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡
17) የመንግስት ተሿሚዎች ደመወዝ ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም በቁጥር መ30-899/4 በጠቅላይ ሚንስቴር ፅ/ቤት በተገለፀዉ መሰረት ለተሾሙበት የሹመት ደረጃ ወይም ለተሾሙበት የመንግስት መስሪያቤት የተፈቀደዉን ብቻ የሚከፈል ይሆናል፡፡ ከዚህ ዉጭ ተፈፃሚ ያደረገ አካል ተጠያቂ ይደረጋል፡፡
18) የዳኞችና የዐቃቢ ህግ ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች የክፍያ ሁኔታ በመንግስት ሰራተኞች የክፍያ ስኬል መሰረት መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በክልልም ሆነ በፌደራል አፈፃፀሙ በዚሁ መሰረት ይሆናል፡፡
19) አንድ ሰራተኛ የሚከፈለዉ ደመወዝ በሁለት የእርከን ደመወዞች መካከል ካረፈ ደመወዙ አቅራቢያዉ ወዳለዉ ከፍያለ እርከን ወይም የጣሪያ ደመወዝ ላይ እንዲያርፍ ይደረጋል፡፡

ክፍል አራት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
5. ስለአባሪ
ከዚህ መመሪያ ጋር አባሪ የተደረገው የደመወዝ ስኬል ሰንጠረዝ የመመሪያው አካል ተደርጎ ይወሰዳል
6. ተፈፃሚነት ስለማይኖራቸው ህጎች
ከዚህ መመሪያ ጋር የሚቃረን ማንኛውም መመሪያ ወይም ልማዳዊ አሠራር በዚህ መመሪያ ውስጥ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም።

7. ተጠያቂነት
የዚህ መመሪያን ድንጋጌዎች በመተላለፍ፣ በመመሪያው ከተመለከተው ሥርዓት ውጭ የኑሮ ውድነት ማካካሻ ክፍያ የሚፈጽም ኃላፊ አግባብ ባለው ህግ ተጠያቂ ይሆናል፡፡
8. በዚህ መመሪያ ያልተሸፈኑ ጉዳዮች
በዚህ መመሪያ ያልተሸፈኑ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ጥያቄው ለኮሚሽኑ እየቀረበ ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናል።

9. መመሪያውን ስለማሻሻል
በሥራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችንና ክፍተቶችን ለመፍታት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኝ ኮሚሽኑ የማስፈጸሚያ መመሪያውን ሊያሻሽል ይችላል።

10. መመሪያው ተፈፃሚ የሚሆንበት ጊዜ
ይህ መመሪያ በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጸድቆ በፍትህ ሚኒስቴር ከተመዘገበና በተቋሙ ድረገጽ ከተጫነበት ቀን ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
አዲስ አበባ፣ መስከረም 2018
መኩሪያ ኃይሌ (ፒ.ኤች. ዲ)
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር

