Header Topbar

የኮንስትራክሽን ውል የተደረገበት ቀን እና በኮንስትራክሽን ውል የስራ መጀመሪያ ቀን – Contract signing date and Commencement date

Construction

የኮንስትራክሽን ውል የተደረገበት ቀን/contract signing date እና በኮንስትራክሽን ውል የስራ መጀመሪያ ቀን/Commencement date

Thank you for reading this post, don't forget to subscribe!Thank you for reading this post, don't forget to subscribe!

=================

በኮንስትራክሽን ውል ውስጥ የስራ መጀመሪያ ቀን እና ውል የተደረገበት ቀን የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ይሄውም የሆነበት ውሉ በተደረገበት እለት የግንባታ ስራ ይጀመራል ተብሎ ስለማይታሰብ ነው፡፡

In a construction contract, the date of commencement of work and the date of contract are different matters. This is because it is not expected that construction work will start on the day the contract is signed.

                ——-///——-///—–

በኮንስትራክሽን ውል የስራ መጀመሪያ ቀን/Commencement date/

-በመርህ ደረጃ የውል የግንባታ ስራ ማከናወኛ የጊዜ ገደብ መቆጠር የሚጀምረው ከኮመንስመንት ዴት ጀምሮ ነው፡፡ ስለዚህ የውሉ የግንባታ ጊዜ ተብሎ የሚጠቀሰውን ቀን ውሉ ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ መቁጠር ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም የኮንስትራክሽን ውል በአሰሪና ተቋራጭ መካከል ከተፈረመ በኋላ የግንባታው ተጨባጭ ስራ በተለያየ ምክንያት ሊዘገይ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ግንባታው የሚከናወንበት ቦታ የይገባኛል ጭቅጭቅ ቢነሳበት ጭቅጭቁ እስኪፈታ ድረስ አሰሪው የግንባታውን ሳይት ለተቋራጩ ማስረከብ ያልቻለ እንደሆነ ግንባታው ችግሩ እስከሚፈታ ድረስ ሳይጀመር መቆየቱ የማይቀር ይሆናል፡፡ ለተቋራጩ የሳይት ርክክብ/site handover/ ካልተፈጸመለት ስራ መጀመር አይችልም፡፡ ስለዚህ ተቋራጩ ሳይት ሳይረከብ የግንባታውን ጊዜ መቁጠር ተገቢነት የለውም፡፡ እንደዚሁም ተቋራጩ የግንባታ ቁሳቁስ እና የሰው ሀይል ሞቢላይዝ እስከሚያደርግበት ምክንያታዊ ጊዜ ድረስ የስራ መጀመሪያ ቀን ሊጀምርበት አይገባም፡፡

-በዚህ ረገድ በተግባር አልፎ አልፎ ስህተት ሲሰራ ይስተዋላል፡፡ ይሄውም አሰሪዎች አንዳንዴ የግንባታውን ጊዜ ውሉ ከተደረገበት ቀን ጀምረው በመቁጠር እና ተቋራጩን በቂ ምክንያት ካለህ የጊዜ ማራዘሚያ/Time extension/ ጠይቅ የሚሉበት ሁኔታና አጋጣሚ አለ፡፡ ይሄ ተገቢ አሰራር አይደለም፡፡

-በዚህ ረገድ በሀገራችን እና በአለም ሀገራት እየተሰራባቸው ያሉ የዳበሩ የፊዲክ ጀኔራል ኮንዲሽኖች እና በሀገራችን ተጣጥመው የተቀረጹ ጀኔራል ኮንዲሽኖች ምን ይዘት አላቸው የሚለውን እና የፍትሀብሄር ህግ ድንጋጌዎችን ደግሞ ቀጥለን እንዳስሳለን፡፡     

FIDIC RED BOOK 1999

-በፊዲክ ሬድ ቡክ 1999 ቨርሽን ክሎስ 8.1 ላይ ኢንጅኒየሩ ለተቋራጩ ስራ እንዲጀምር ማስታወቅ እንዳለበት እና ከ7 ቀን ያላነሰ ጊዜ መስጠት እንደሚገባው ይጠቅሳል፡፡ እንደዚሁም በስፔሻል ኮንዲሽን ኦፍ ኮንትራክት በልዩ ሁኔታ ካልተቀመጠ በስተቀር የስራ መጀመሪያው ቀን/ Commencement date/ ተቋራጩ በጨረታው አሸናፊነቱ ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ በ42 ቀናት ውስጥ መሆን እንዳለበት ተቀምጧል፡፡ በተጨማሪም ተቋራጩ ከስራ መጀመሪያ ቀን በኋላ ወዲያውኑ እና ያለመዘግየት የግንባታ ስራ መጀመር እንዳለበት ይገልጻል፡፡

-ተቋራጩ/contractor/ ከስራ መጀመሪያ ቀን በኋላ ይቅርታ ሊያሰጥ የሚችል ምክንያት ሳይኖረው ያለመዘግየት የግንባታ ስራ መጀመር እንዳለበት በክሎስ 8 ላይ የተቀመጠውን ግዴታውን ያልተወጣ እንደሆነ ደግሞ አሰሪው/client/ ውሉን ለማቋረጥ እንደሚችል ክሎስ 15.2(c) ላይ ተቀምጧል፡፡

FIDIC 1987

-በኮንዲሽን ኦፍ ኮንትራክት ፎር ወርክስ ኦፍ ሲቪል ኢንጅነረንግ ኮንስትራክሽን ፊዲክ 1987 ቨርሽን ክሎስ 41.1 ላይ ስለ ኮመንስመንት ዴት/የስራ መጀመሪያ ቀን ተቀምጧል፡፡ ይዘቱም መሀንዲሱ የስራ መጀመሪያውን ቀን በጨረታ ሰነዱ አፔንዴክስ ላይ በተገለጸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለተቋራጩ ማስታወቅ እንዳለበት የሚገልጽ ነው፡፡ ተቋራጩም የስራ መጀመሪያው ቀን በመሀንዲሱ ከተገለጸለት በኋላ ያለመዘግየት እና በተቻለ ፍጥነት የግንባታ ስራውን መጀመር እንዳለበት ይገልጻል፡፡ የግንባታ ማጠናቀቂያ ቀን/completion date/ መቆጠር የሚጀምረውም ከኮመንስመንት ዴት ጀምሮ ስለመሆኑ ክሎስ 43.1 ላይ ተቀምጧል፡፡

-እንግዲህ ተቋራጩ በቂ ምክንያት ሳይኖረው በክሎስ 41.1 ላይ በተመለከተው አግባብ የግንባታ ስራውን ሳይጀምር የቀረ እንደሆነ አሰሪው የ14 ቀን ማስጠንቀቂያ በመስጠት ውሉን ለማቋረጥ እና ተቋራጩን ከሳይት ለማስወጣት መብት/expel right/ እንዳለው ክሎስ 63.1 ያስቀምጣል፡፡

MoWUD 1994

-ይህ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በ1994 ስራ ላይ አውሎት የነበረው የሲቪል ግንባታ ስራዎች ቋሚ የውል መተዳደሪያ/MoWUD 1994/ በተለይ ከፊዲክ/FIDIC 1987 ቨርሽን የተወሰደ ሲሆን ስለኮመንስመንት ዴት በሁለቱም ጀኔራል ኮንዲሽኖች ላይ ተመሳሳይ ይዘት ባለው ሁኔታ ያስቀምጣሉ፡፡ ስለዚህ ማብራሪያውን መድገም አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም፡፡

PPA 2011

-በፒፒኤ 2011 ቨርሽን ክሎስ 71 ላይ የስራ መጀመሪያ ቀን በስፔሻል ኮንዲሽን ኦፍ ኮንትራክት ላይ ሊቀመጥ እንደሚችል ወይም ደግሞ በአስተዳደራዊ መንገድ በኢንጅኒየሩ በሚሰጥ ትእዛዝ ሊታወቅ እንደሚችል ይጠቅሳል፡፡

-እንዲሁም በሌላ ሁኔታ በውሉ ላይ ካልተገለጸ በስተቀር ለተቋራጩ የጨረታ አሸናፊነቱ ከተገለጸ ቀን ጀምሮ ታስቦ ከ120 ቀናት ለማለፍ አይችልም፡፡

የፍትሀብሄር ህግ

-የስራ ማከናወኛ ውል(የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 2610-2637) በሚመለከት በውሉ ላይ የጊዜ ጉዳይ በግልጽ ያልተጠቀሰ እንደሆነ ተቋራጩ ወዲያውኑ ስራ መጀመር እንደሚኖርበት በአንቀጽ 2619 ላይ ተደንግጓል፡፡ የግንባታ ጊዜ በተገለጸባቸው ውሎች ደግሞ ስራ ተቋራጩ ስራውን ወዲያው ያልጀመረ እንደሆነ እና በጊዜ ገደቡ የግንባታ ስራውን ለመፈጸም የማይችል መሆኑ የታወቀ እንደሆነ አሰሪው ለተቋራጩ ስራውን የሚጀምርበትን ጊዜ ሊወስንለት እንደሚችል በአንቀጽ 2618 ላይ ተቀምጧል፡፡ ሌላው እነዚህ ደንቦች ስለማይንቀሳቀስ ንብረት ስራ ውል(የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3019-3040) በሚመለከተው የግል የስራ ተቋራጭነት ውል ላይ ጭምር ተፈጻሚነት እንደሚኖራቸው ከአንቀጽ 3019(2) ድንጋጌ መገንዘብ ይቻላል፡፡ 

-የአስተዳደር መስሪያ ቤት የኮንስትራክሽን ውል ማለትም የመንግስት ስራዎች መቋረጥ ውል(የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3244 እና ተከታዮቹ) በሚመለከት እያንዳንዱ ተዋዋይ ወገን ግዴታዎቹን በውሉ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ መፈጸም ይኖርበታል፡፡ በውሉ ላይ ግልጽ የጊዜ ስምምነት የሌለ እንደሆነ ደግሞ ግዴታው በአእምሮ ግምት በቂ በሆነ ጊዜ መፈጸም እንደሚኖርበት በአንቀጽ 3174 ላይ ተቀምጧል፡፡ ይህ ድንጋጌ ስለአስተዳደር መስሪያ ቤት ውሎች በጠቅላላው የተደነገገ ሲሆን የመንግስት ስራዎች መቋረጥ ውልን በሚመለከተው ልዩ ክፍል ላይም በግልጽ ስለስራ ጊዜ ተደንግጓል፡፡

-ይሄውም በኮንስትራክሽን ውሉ ላይ የግንባታ ስራዎቹ በሙሉ የሚከናወኑበት ጠቅላላው ጊዜ ብቻ ተጠቅሶ እንደሆነ አሰሪው መስሪያ ቤት/client/ የግንባታ ስራው የሚጀመርበትን ጊዜ/ Commencement date/ ዘርዝሮ ለተቋራጩ ማስታወቅ እንዳለበት በፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3253(2) ላይ ተደንግጓል፡፡  

            ———///———///———-

የኮንስትራክሽን ውል የተደረገበት ቀን/contract signing date

-የኮንስትራክሽን ውል ስምምነት/contract agreement በአሰሪ/client እና በተቋራጭ/contractor መካከል የሚፈረምበት ቀን የኮንስትራክሽን ውል የተደረገበት ቀን/contract signing date/ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

-እዚህ ላይ የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3020 ድንጋጌ እና አንድ ውል ተቋቋመ ሊባል የሚችለው መቸ ነው? የሚለው ማለትም የውል አቀራረብ/offer እና አቀባበል/acceptance በሚመለከት በፍትሀብሄር ህጉ 1681 እና ተከታዮቹ የተደነገገው እና የውል ፎርም ጉዳይ ከግምት ውስጥ መግባት ጭምር አለበት፡፡

-የግል የኮንስትራክሽን ውል ጉዳዮችን በሚመለከተው የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3020(1) ላይ አሰሪና ተቋራጭ ስለሚሰራው ስራ እና ስለዋጋው ካልተስማሙ በስተቀር የተቋራጭነት ውል አለ እንደማይባል ተደንግጓል፡፡

-ሌላው ከአስተዳደር መስሪያ ቤት ጋር የሚደረጉ ውሎችን በሚመለከት ስለውሎች በጠቅላላው የተደነገገው ጭምር ተፈጸሚነት እንዳለው የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3131(1) ይደነግጋል፡፡ የአስተዳደር መስሪያ ቤት ውሎች በጽሁፍ መደረግ እንዳለባቸው በፍትሀብሄር ህግ ስለውሎች በጠቅላላው በሚደነግገው ክፍል በአንቀጽ 1724 ላይ ተደንግጓል፡፡

-የውልን ጉዳይ ስለሚመለከት ማስረጃ በፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 2005(1) ላይ እንደተደነገገው ደግሞ የጽሁፍ ሰነድ በላዩ ላይ የተጻፈውን ቀን በሚመለከት በተፈራራሚዎች መካከል ሙሉ እምነት የሚጣልበት ማስረጃ ነው ይላል፡፡

-እንግዲህ ውል የተደረገበት ቀን በአሰሪና ተቋራጭ መካከል የውል ግንኙነት መቋቋሙን ለማረጋገጥ ይጠቅማል፡፡ውል ደግሞ ከተቋቋመበት ቀን ጀምሮ በተዋዋዮች መካከል እንደህግ እንደሚቆጠር የፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 1731(1) ይደነግጋል፡፡ ሆኖም ግን ውሉ የተደረገበት ቀን የውሉ የግንባታ ስራ መጀመሪያ ቀን ተደርጐ ሊወሰድ አይገባም፡፡

            ———///———///———-

በአጠቃላይ የስራ መጀመሪያ ቀን እና ውል የተፈረመበት ቀን ከውል አተገባበር ጠቀሜታ አንጻር የተለያየ ፋይዳ ያላቸው ናቸው፡፡ የውሉን የስራ ጊዜ በተለይ ውሉ ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ መቁጠር ተገቢነት የለውም፡፡ ኮመንስመንት ዴት የውሉን የግንባታ ማከናወኛ ጊዜ ለመቁጠር እንደመነሻ ተደርጐ ሊወሰድ ይገባል፡፡ የግንባታ ማጠናቀቂያ ጊዜ/completion date/ ትክክለኛ ቀን ተሰልቶ መታወቅ ያለበት ከኮመንስመንት ዴት ጀምሮ ቀኑ ተቆጥሮ መሆን አለበት፡፡የውሉን ጊዜ ለማስላት ውሉ ከተፈረመበት ቀን የተጀመረ እንደሆነ ግን የግንባታ ማጠናቀቂያ ቀን የማሳጠር ውጤት ስለሚኖረው እና ይሄውም ተቋራጩን አላግባብ የመዘግየት ቅጣት/ሊኩዴትድ ዳሜጅ/ እንዲጀመርበት ስለሚያደርግ እና ወደ አለመግባባት ስለሚያመራ ውሉ የተደረገበትን ቀን እና ኮመንስመንት ዴት ልዩነት በሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

                   አመሰግናለሁ

በጉባኤ አሰፋ (ጠበቃ እና የህግ አማካሪ

የኮንስትራክሽን ውል የተደረገበት ቀን እና በኮንስትራክሽን ውል የስራ መጀመሪያ ቀን – Contract signing date and Commencement date
Spread the love
Scroll to top

You cannot copy content of this page